News
ኦሞ ባንክ አ.ማ. አዲስ የዲጂታል ሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ በይፋ ስራ አስጀመረ
ኦሞ ባንክ አ.ማ. አዲስ የዲጂታል ሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ በይፋ ስራ አስጀመረ፡፡
28/6/2018 ዓ/ም አዲስ አበባ፡-
ኦሞ ባንክ አ.ማ. በዛሬው ዕለት የስትራቴጂክ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ዋና ክፍል የሆነውን የዲጂታል ሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ በስካይላይት ሆቴል በድምቀት አስመርቆ ለደንበኞች አገልግሎት አበቃ፡፡
የኦሞ ባንክ ተ/ፕሬዝዳንት አለማየሁ ኃ/ጊዮርጊስ በዲጅታል ሞባይል ባንኪንግ መተግበርያ ሥነ-ስርዓት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸው ይህ አዲስ የዲጂታል ሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ የደንበኛ አገልግሎትን ቀልጣፋና የተሳለጠ እንዲሆን በማስቻል የደንበኛን ጊዜ እና እንግልት የሚያቀል በመሆኑ የደንበኞቻችንን ሁሉን በአንድ ያሟላ የዲጂታል አገልግሎት ጥያቄ በአግባቡ የሚመልስ ነው ብለዋል፤ አያይዘውም ወቅቱን የሚዋጅ የባንኩን የኢንዱስትሪ ተወዳዳሪነትና የገበያ ድርሻ የሚያሳድግ ፈርጀ ብዙ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
በዲጅታል ሞባይል መተግበርያው ስነ_ስርዓት ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኦሞ ባንክ የቦርድ አመራርና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግና የፋይናንስ ቢሮ ሀላፊ አቶ ተፈሪ አባተ ኦሞ ባንክ ከ25 ዓመታት በላይ በኢትዮጵያ በቀድሞ በደቡብ ክልል የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየ ባንክ እንደሆነ ገልጸው የባንክ አገልግሎቶችንና የማይክሮ ፋይናንስ አገልግሎቶችንዠዠ በማጣመር የአገልግሎትአሰጣጡን በዲጂታል መንገድ በመስራት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ኦሞ ባንክ የዲጂታል አገልግሎቶችን ማስተዋወቁ እንደ ሀገር የተያዘውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ትግበራ የሚያግዝ እንደሆነም ገልጸዋል።
አዲሱ የዲጂታል ሞባይል ባንኪንግ መተግበሪያ ከኦሞ ባንክ ወደ ሌላ ኦሞ ባንክ ሒሳብ እንዲሁም ወደ ማንኛውም ባንክ ገንዘብ ማስተላለፍ፤ የብድር አገልግሎት፣የቼክ አገልግሎት፣ የባንክ እስቴትመንት ማውረድ፣የአገልግሎት ክፍያ፤ የግዢ ክንውን፤ የሞባይል የአየር ሰዓት ግዢ፤ ከቴሌብር ጋር የተሳሰረ እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የባንክ አገልግቶችን የሚያቀላጥፍ ፈጣን ቀላል መላ መሆኑን የባንኩ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ሲኒየር ዳይሬክተር፤ አቶ ዘሪሁን ፈጠን ገለጻ አድርገዋል፡፡
እንዲሁም አዲሱ አገልግሎት በቀጣይ ሌሎች እንደ ዲጂታል ብድር የመሳሰሉትን በማካተት አገልግሎቱን እያሰፋ እንደሚሄድ ተገልጿል፡፡
በመድረኩ ማጠቃለያም ኦሞ ባንክ ምርትና አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽና አካታች በማድረግ የደንበኞችን አገልግሎት የተቀላጠፈና ፈጣን ለማድረግ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን የኦሞ ባንክ የቦርድ አባልና የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ተፈሪ አባተ አሳውቀዋል፡፡
ኦሞ ባንክ
የሁላችንም ባንክ!!


