News
ኦሞ ባንክ በክልሉ ማኅበረሰብ ዘንድ ለቁጠባ ባህል መስፋፋት መሠረት የጣለ ነው – አቶ ፍቅሬ አማን፤ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን፣ ከኦሞ ባንክ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ስትራቴጂካዊ አጋርነትን ለማጠናከር ያለመ ውይይት በጽሕፈት ቤታቸው አካሂደዋል።
የርዕሰ መስተዳድሩ አስተያየት
በውይይቱ ወቅት አቶ ፍቅሬ እንደገለጹት፣ ኦሞ ባንክ ቀደም ሲል የማይክሮ ፋይናንስ ተቋም በነበረበት ወቅት በዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ውስጥ ለነበሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤ ለቁጠባ ባህል ማደግም መሠረት ጥሏል።
ባንኩ በአሁኑ ወቅት ወደ ሙሉ የባንክ አገልግሎት ሰጪነት አድጎ የጀመራቸውን አዳዲስ አሠራሮች የክልሉ መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚደግፍ ርዕሰ መስተዳድሩ አረጋግጠዋል።
ለባንኩ የተጠቆሙ ጉዳዮች
ርዕሰ መስተዳድሩ ባንኩ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቁመዋል።
የምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አስተያየት
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው፣ ባንኩ ውስጣዊ አቅሙን በማጠናከር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀምና ብቁ የሰው ኃይል በማደራጀት ተወዳዳሪ የባንክ አገልግሎት ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል።
ባንኩ የጀመራቸውን የሪፎርም ሥራዎች የክልሉ መንግሥት እንደሚደግፍ የጠቆሙት አቶ ማስረሻ፣ በተለይም የሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት አሠራርን በመተግበር የክልሉን አርሶ አደር ተጠቃሚ ማድረግ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
የኦሞ ባንክ ፕሬዝዳንት ጥሪ
የኦሞ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ ብሩክ ዋለልኝ በበኩላቸው፣ የባንኩን የቀጣይ ስትራቴጂካዊ ዕቅዶች በዝርዝር አቅርበዋል። የክልሉ መንግሥት ከባንኩ ጋር ያለውን ሁለገብ አጋርነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።
ክልሉ የባንኩ ደጀን በመሆን ከባንኩ ጎን እንዲቆም የጠየቁት አቶ ብሩክ፣ ለጋራ ብልጽግና በአብሮነት መሥራት እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኦሞ ባንክ — የሁላችንም ባንክ!





